የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጌታሁን የኮንሶ ሙዚየምና ጥናት ማዕከል የጥገና ሥራን ተመልክተዋል።
የኮንሶ ሙዚየምና ጥናት ማዕከል ዋና ሙዚየም በተሳካ ሁኔታ መታደሱ ተገልጿል።
የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ እና የኮንሶ ዞን አስተዳደር ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በተደረገ ጠንካራ ትብብር፣ 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በመጠቀም የዋናው ሙዚየም የመጀመሪያ ዙር የጥገና ሥራ መጠናቀቁን አቶ ተካልኝ ጌታሁን ገልፀው፤ እንዲሁም ሙዚየሙ ለህዝብና ለጎብኚዎች ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። በሙዚየሙ የኮንሶ ብሔር ባህላዊ ትውፊትን የሚያሳዩ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው በርካታ ቅርሶች በተደራጀ መልኩ መሰብሰባቸውና መቀመጣቸው፣ ለሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የኮንሶ ሙዚየሙ ዳይሬክተር አቶ ኡርማሌ ጭውሌ በበኩላቸው፣ ከፈረንሳይ ኤምባሲ በተገኘው ድጋፍ የሙዚየሙ ጣሪያ፣ የዝናብ ውሃ ማስወገጃ ስርዓት፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች እና የህንጻው አጠቃላይ ገጽታ ለጎብኚዎች ተስማሚ እንዲሆን መጠገኑን ገልጸዋል። ቀሪ የጥገና ፍላጎቶች መካከል ወደ ሙዚየሙ የሚወስድ መንገድ ጥገና፣ የዕደ ጥበብ ማዕከላት እና የሙዚየሙ ቢሮዎች ተጨማሪ ጥገና እንዲያገኙ ጠይቀዋል።በሙዚየሙ የሚገኙ ቅርሶች ለመማርና ለማስተማር፣ ለምርምር እንዲሁም ለጎብኚዎች እንዲያገለግሉ በተገቢው መልኩ መደራጀታቸውንም አቶ ኡርማሌ ጭውሌ አስታውቀዋል።
በመጨረሻ፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተካልኝ ጌታሁን በሙዚየሙ የተከናወኑትን የጥገና ሥራዎች በመዘዋወር ከተመለከቱ በኋላ፣ በቀጣይ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ግብረ-መልስ ሰጥተዋል።
በዚህም፣ ከአስፋልቱ እስከ ሙዚየሙ የሚወስደው መንገድ በዞኑና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በአስቸኳይ እንዲጠገን እና በኮንሶ እርከን ጥበብ እንዲዋብ መመሪያ በመስጠት፣ የሙዚየሙ ግቢ ለጎብኚዎች ውብና ጽዱ እንዲሆን አሳስበዋል። እንዲሁም፣ በሙዚየሙ ያለው የዕደ ጥበብ ማዕከል ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በተጀመረው ትብብር ድጋፍ እንደሚጠገን አቶ ተካልኝ ገልፀው፣ ቀሪው የሙዚየሙ የጽ/ቤት ጥገና እና የቅርሶች ማስቀመጫ ሸልፎች ስራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
